ሰኔ 20/2016 ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሴቶች በሴቶች ልማት ህብረት ታቅፈው ኢኮሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ። ቢሮው በገቢ ማስገኛ ለተሰማሩ የሴቶች ልማት ህብረቶች ልዩ ልዩ ድጋፎችን አድርጓጋል። በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሴቶች አዲስ በተፈጠረው የሴቶች ልማት ህብረት አደረጃጀት ስር ታቅፈው ኢኮሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የክልሉ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ አስታውቋል። ቢሮው በልማት ህብረት ስር በተለያዩ ገቢ ማስገኛ ስራዎች ለተሰማሩ ሴቶች አንድ ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ልዩ ልዩ ድጋፎችን አድርጓል። የቢሮው ሃላፊ ወ/ሮ በይዴሙንዲኖ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በሴቶች ልማት ህብረት ስር የተደራጁ ጠንካራ የክልሉ ሴቶች በአዲስ መልክ እየተካሄደ ባሉ የሌማት ትሩፋትና ምግቤን ከጓሮዬ የልማት ንቅናቄዎች ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ። ይህም ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን በማሳደግ በኩል ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ሃላፊዋ ተናግረዋል ።በክልሉ ከአንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሺ በላይ የሚሆኑ ሴቶች በአንድ ለአስርና አንድ ለሰላሳ ልማት ህብረት ስር መደራጀታቸውን የጠቆሙት ወ/ሮ በይዴ ይህ እንቅስቃሴ የሴቶችን ገቢ በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ አቅም እንደሚያጎለብት ገልጸዋል። ይህም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግርን ከመቅረፍ ባለፈ የውሳኔ ሰጭነት ሚናቸውን ያጎለብታል ብለዋል። ቢሮው የሴቶችን መብትና ደህንነት በማስጠበቅ ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ሴቶች በየተሰማሩበት የስራ መስክ አርኣያ ሆነው የልማት ንቅናቄዎችን እንዲመሩና የህጻናትን ደህንነትና መብት በማስጠበቅ በኩል የድርሻቸውን እንዲወጡም ወ/ሮ በይዴ ጥሪ አቅርበዋል ። የቢሮው ምክትልና የሴቶች ዘርፍ ሃላፊ ወ/ሮ ፈቲያ ጀማል በበኩላቸው በክልሉ በሴቶች ልማት ህብረት የተደራጁ በንቅናቄ ለሚካሄዱ የጤናና የግብርና ስራዎች ስኬታማነት ግንባር ቀደም ሚና እየተወጡ ይገኛሉ ብለዋል። በተለይም ደግሞ በሌማት ትሩፋት፣ በጓሮ አትክልት ልማት፣ በእንስሳት እርባታ፣ በቁጠባና የትምህርት ስራዎችን በመደገፍ ረገድ የማይተካ ሚና እየተወጡ መሆኑን አስረድተዋል። በቁጠባ ረገድ 456 ሚሊየን ብር የክልሉ የሴቶች ልማት ህብረት መቆጠቡን የተናገሩት ወ/ሮ ፈቲያ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ለትምህርት ግብኣት የሚሆን 27 ሚሊዮን ብር ማበርከታቸውንም አስረድተዋል። ለልማት ህብረቶቹ ከ304 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር መቅረቡንም ምክትል ሃላፊዋ ተናግረዋል። ቢሮው በዛሬው እለት ለክልሉ ሴቶች ህብረት የተለያዩ የጓሮ አትክልት ዘሮች፣የንጽህና መጠበቂያ ለ11 ትምህርት ቤቶች የሚኒ ሚዲያ መሳሪያዎች፣ለሴት ተማሪዎች የሚሆን ደብተር፣ እስኪርቢቶ፣ሳሙናና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል። ድጋፉ ከተባበሩት መንግስታት የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ እድሜ ጋብቻ ማስቆም ፕሮግራም የተገኘ ሲሆን አንድ ሚሊዮን ብር እንደሚገመት ለማወቅ ተችሏል። በዳውድ አብደላ