Skip to main content
zena6

ሰኔ 18/2016 በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የሁሉንም አካላት የጋራ ጥረት እንደሚጠይቅ ተጠቆመ። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶች እና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ከክልሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት አስወጋጅ ጥምረት ጋር በወራቤ ከተማ የምክክር መድረክ ተካሂዷል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶች እና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ባይዳ ሙንዲኖ በምክክር መድረኩ ላይ እንደገለጹት በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ለመከላከል የሁሉንም አካላት የጋራ ጥረት ይጠይቃል ብለዋል። ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት የሴቶችን ጤና፣ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊ እና ሁለንተናዊ ህይወት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ስለመሆኑም ጠቁመዋል። በክልሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን መከላከል እና ተከስቶም ሲገኝ ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚገባ የተናገሩት ኃላፊዋ በክልሉ በ2017 ዓም የሴቶች ግርዛት እና ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስወገድ እየተሰራ ነው ብለዋል። የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ በትብብር እና በቅንጅት መስራት እንደሚገባም ወ/ሮ ባይዳ አስረድተዋል። በክልሉ የሴት ልጅ ግርዛት እና ያለ እድሜ ጋብቻን ከመከላከል አንጻር ስልጤ፣ሀዲያ እና ከምባታ ዞኖች የተሻለ ተሞክሮ እንዳላቸውም ኃላፊዋ በአብነት ጠቅሰዋል። ህብረተሰቡ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን መከላከል እንዲችል የታችኛውን መዋቅር ያካተተ የንቅናቄ መድረክ መዘጋጀቱንም አብራርተዋል። በክልሉ በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚከሰተውን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት በዘላቂነት ለመከላከል ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ የትብብር ኮሚቴዎችን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑንም ወ/ሮ ባይዳ በንግግራቸው አብራርተዋል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶች እና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የሴቶች ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ፈቲያ ጀማል እንደገለጹት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊትን ለመከላከል ባለ ድርሻ አካላትን ያሳተፈ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል። ህብረተሰቡ በዘርፉ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው እስከ ታችኛው መዋቅር የንቅናቄ ስራዎች ተግባራዊ ስለመደረጋቸው የተናገሩት ምክትል ኃላፊዋ በዚህም ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ መምጣቱን አብራርተዋል። በክልሉ በየደረጃው በተደረገ ቅንጅታዊ አሰራር ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ነጻ የሆኑ ቀበሌዎችን መፍጠር መቻሉን የተናገሩት ወ/ሮ ፈቲያ የተሻለ ተሞክሮ ያለባቸውን አካባቢዎች ወደ ሌሎች ለማስፋፋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶች እና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የህጻናት ዘርፍ ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ እየሩሳለም ወንድ ወሰን በበኩላቸው በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመከላከል በዘርፉ የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ የተጀመረው ጥረት ውጤታማ ነው ብለዋል። በክልሉ ወደ ጎዳና የወጡ 432 ህጻናት ተለይተዋል ያሉት ወ/ሮ እየሩስ የስብዕና ግንባታ ማዕከላት አለመኖር በዘርፉ ለሚደረገው ጥረት ተጎዳሮት መሆኑን አመላክተዋል። የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች እንደገለጹት በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በመከላከል ረገድ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማጎልበት ይገባል ብለዋል። በመድረኩ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል ቅንጅታዊ ምላሽ ለመስጠት እና በዘላቂነት ለማስወገድ ክልላዊ የትብብር ጥምረት የጋራ መግባቢያ ሰነድ የፊርማ ስነ ስርዓት ተካሂዷል። በተስፋዬ መኮንን