የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች ቢሮ ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር የሴት ልጅ ግርዛትንና ያለዕድሜ ጋብቻን ለመከላከል የአሰልጣኞች ስልጠና በቦኖሻ ከተማ እየሰጠ ይገኛል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊና የሴቶች ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ፈቲያ ጀማል በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ በተለይም የሴት ልጅ ግርዛትና ያለዕድሜ ጋብቻን ለማስቆም የመላው ማህበረሰብ ውይይትና ተሳትፎ ሚናው የጎላ መሆኑን በስልጠናው መክፈቻ ወቅት ገልጸዋል። በወረዳው በአዲስ መልክ ተከስቶ የነበረውን የሴት ልጅ ግርዛት በባለድርሻ አካላት ርብርብ ጋብ ማለቱንም ጠቁመዋል። የዩኒሴፍ የአካባቢው ጽ/ቤት የህጻናት ጥበቃ አስተባባሪ ወ/ሮ ሩት ረጋሳ በበኩላቸው በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ እንደ የሴት ልጅ ግርዛት ያሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በመሆናቸው በህግ እንደሚያስጠይቁ ታውቆ በትኩረት መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል። በወረዳው በአዲስ መልክ ተከስቶ የነበረውና ቀደም ሲል በባለድርሻ አካላት ርብርብ መቀነስ የተስተዋለበት የሴት ልጅ ግርዛት ህብረተሰቡ አምኖበት በመከላከል ማስቀረት እንዲቻል ስልጠናው መሰጠት አስፈልጓልም ነው የተባለው። በስልጠናው አዋቂ ወንዶችና ሴቶች ፣ ልጃገረዶችና ወጣቶች ተሳታፊ ሲሆኑ በየቀበሌው በመሄድም የማህበረሰብ ውይይት በማመቻቸት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ታውቋል።