የስርዓተ ጾታ አድሎዎችን በማስቀረት በከተሞች የመሰረተ ልማት መስፋፋት የሴቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ለነገ የሚባል ተግባር አይደለም - የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች ቢሮ ገለጸ! የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሴቶችና ህጻናት ቢሮ በክልሉ ከተሞች የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያለመ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በቡታጀራ ከተማ አካሂዷል። የክልሉ ሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊና የሴቶች ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ፈቲያ ጀማል በከተማ መሰረተ ልማትና የተቋማት ግንባታ ላይ የስርዓተ ጾታ አድልዎ እንደሚስተዋል በመጠቆም ይህንን አድልዖ በማስቀረት የሴቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ በመክፈቻ ንግግራቸው ገልጸዋል። በክልሉ ሴቶች የህብረተሰቡን ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ቁጥር ይሸፍናሉ ያሉት ወ/ሮ ፈቲያ በመሆኑም ለክልሉ ብሎም ለሀገር ብልጽግና ተሳትፏቸው ወሳኝ ነውም ነው ያሉት። ሁሉንም ልማትና እድገት በስርዓተ ጾታ እይታ እንዲቃኝ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ኃላፊዋ ተናግረዋል። በመድረኩ በከተሞች የመሰረተ ልማትና ተቋማት እድገት ፕሮግራም /UIIDP/ የስርዓተ ጾታ ማካተት እንዲሁም በሴቶች ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ዙሪያ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል። በፕሮግራሙ የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከፍተኛ ትኩረት የተቸረው በመሆኑም ሴቶችን በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፍ ማሳተፍ የሀገር ብልጽግና ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባም በስልጠናው ተብራርቷል። በክልሉ ለሚገኙ ዘጠኝ ከተሞች የስርዐተ ጾታና የዩአይዲፒ ፕሮግራም አስተባባሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ተሳታፊዎች ሲሆኑ የመሰረተ ልማት መስፋፋት ለተስተካከለ የስርዓተ ጾታ ግንባታ ወሳኝ መሆኑን በማስታወስ በከተሞች የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት መረጋገጥ ጠንክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።